በመሠረቱ፣ ማንም ሰው ዕዳ ውስጥ መግባት አይፈልግም። ምክንያቱም፣ ዕዳ አስጨናቂ ነው። ነፃነትንም ያሳጣል። ዕዳ ሲኖር በገንዘብ ዙሪያ ዕቅድ ለማቀድም ሆነ የታቀደውን ከግብ ለማድረስ አስቸጋሪ ይሆናል።

ዕዳን የማስወገድ ዋናው ዘዴ መጀመሪያውኑ ዕዳ ውስጥ አለመግባት ነው። ከተገባ ደግሞ በፍጥነት የሚወጣበትን መንገድ ውይም ዘዴ ማወቅ ያስፈልጋል። ነገር ግን ብዙዎቻችን ዕዳ ውስጥ የገባነው ይህንን ሳናውቅ ቀርተን ሳይሆን የገቢ ማነስ፣ የኑሮ ውድነት፣የእርስ በእርስ ፉክክር፣ ድንገተኛ ወይም ያልታሰበ ወጪ እና የመሳሰሉ የዕዳ ወጥመዶች ውስጥ በተደጋጋሚ እየገባን ራሳችንን ስለምናገኘው ነው። የዕዳ ማጥ ውስጥ ገብተው መውጣት ላቃታቸው እና ዕዳን ተሸክመው ከባድ ኑሮን በመግፋት ላይ ላሉ ሁሉ ዛሬ መልካም ዜና ይዘን ቀርበናል!

ከዕዳ ለመውጣት ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን ሰባት ስልታዊ ተሞክሮዎች ቀጥሎ እናያለን። ከእነዚህ ውስጥ አንዱን ወይም ከዚያ በላይ በመጠቀም ከዕዳ ነጻ መውጣት ይቻላል።

1. በመነሻ ክፍያ ወይም minimum payment ብቻ አለመወሰን
ከወርሃዊው ክፍያ (minimum payment) ላይ ጨምሮ በመክፈልና የወለድ ክፍያን መጠን በመቀነስ ዕዳዎን በፍጥነትና በአስተማማኝ መንገድ መቀነስ ይችላሉ።

2. ከትንሽ ወደ ትልቅ የዳ መጠን በመሽጋገር የሚደረግ የዕዳ አከፋፈል ዘዴ ወይም (Snowballing)
መጀመርያ አነስተኛ ዕዳዎ ላይ ያተኩሩ። ከወርሃዊ ክፍያዎ በላይ የቻሉትን የገንዘብ መጠን ጨምረው በየወሩ ይክፈሉ። ሌሎች ዕዳዎች ቢኖርብዎት  መደበኛውን ወርሃዊ ክፍያ (minimum payment)  መክፈል  አያቋርጡ። በዚህ መንገድ ይህችን ትንሿን ዕዳዎን ከፍለው ሲጨርሱ ወደሚቀጥለው በመዞር ላጠናቀቁት ዕዳ ይከፍሉት የነበረውን ክፍያ ቀጣዩ ዕዳ ክፍያ ላይ ጨምረው ተከፍሎ እስከሚያልቅ ይክፈሉ። እሱ ሲያልቅ ክፍያውን ወደሚቀጥለው ዕዳ አዘዋውረው ከወርሃዊው ክፍያ ላይ ጨምረው ይክፈሉ። በዚህ ዘዴ ተጠቅመው ትንንሾቹን የዕዳ ከረጢቶች ባዶ እያደረጉና ወደትልቁ  ቀሪ ዕዳ እየተሸጋገሩ በመክፈል ተራራ ያህል ገዝፎ የሚታየውን ዕዳ ቀስ በቀስ መናድ ይችላሉ።

3. ከፍተኛ ወለድ ያለውን ዕዳ መጀመሪያ የመክፈል ዘዴ
ሦስተኛው ዕዳ መክፈያ ዘዴ ቀደም ብሎ ካየነው (Snowballing) ዘዴ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ መክፈል የምንጀምረው ግን ትልቅ ወለድ ያለውን ዕዳ ነው፡፡ትልቅ ወለድ ያለው ዕዳ በወለዱ ምክንያት ወርሃዊ ክፍያው ትልቅ ስለሆነ የክፍያውን ጊዜ ካላሳጠርነው ብዙ ሊያስወጣን ይችላል። ስለዚህ ትልቅ ወለድ ካለው ዕዳ በተጨማሪ ያሉብንን ዕዳዎች ወርሃዊ ክፍያቸውን(minimum PMT) ሳናቋርጥ፥ ትልቅ ወለድ ያለውን ዕዳ ከወርሃዊ ክፍያው በላይ ጨምረን በመክፈል፥ በየወሩ ለወለድ የምናወጣውን የገንዘብ መጠን በመቀነስ፥  ዕዳውን በፍጥነት ከፍለን መጨረስ እንችላለን። ከጨረስን በኋላ ይከፈል የነበረውን ገንዘብ ሳንቀንስ ወደ ሁለተኛው ትልቅ ወለድ ያለው ዕዳ ላይ አዘዋውረን መክፈል እንቀጥላለን። በዚህ መልክ የቀሩትን  ዕዳዎች ቀስ በቀ በመዝጋት ከዕዳ ነጻ መሆን እንችላለን።

4. ከወርሃዊ ክፍያ በተጨማሪ በማንኛውም ጌዜ የሚደረጉ ክፍያዎች በቀጥታ ወደ ዋና ዕዳ ቅነሳ እንዲሄዱ ማድረግ
ከዕዳ በፍጥነት ለመውጣት አራተኛው ዘዴ ከወርሃዊ ክፍያ ተጨማሪ በተቻለ መጠን ለመክፈል መሞከር ነው። የሚከፈል ማንኛውም ገንዘብ ዋናውን ብድር እንዲቀንስ ያደርገዋል። ይህም ድርጊት የመነሻውን ብድር መጠን እየቀነሰውና የወለዱንም ክፍያ እያሳነሰው ዕዳው ከቀኑ በፊት ተከፍሎ እንዲያልቅ ይረዳዋል። ከመክፈልዎ በፊት ግን ጭማሪው ክፍያ ዋናው ብድር(principal) ላይ መዋል እንዳለበት ላበዳሪው ቀድሞ ማሳወቅ ያስፈልጋል። አንዳንድ አበዳሪዎች ይህ መመሪያ በስልክ ወይም ድረገጻቸው በኩል እንዲደርሳቸው ይፈልጋሉ፤ ሌሎች ደግሞ ተጨማሪ ክፍያ በተደረገ ቁጥር የጽሁፍ ማሳወቂያ ይፈልጋሉ።

5.የውስን ጊዜ ቁርጠኝነት (አባካኝ ልምዶችን በመተው)
ዕዳን በቶሎ ከፍሎ ለመጨረስ 5ኛው ዘዴ የማይጠቅሙ የሚመስሉ ነገር ግን ዕዳችንን ለመክፈል በእጅጉ የሚያግዙ ልምዶችን ማዳበር ነው፡፡

ለምሳሌ፦

  • ከቤት ውጭ የምንመገብባቸውን ቀናት በመቀነስ ያተረፍነውን ገንዘብ ለዕዳ ክፍያ መጠቀም
  • ቡናን እቤት በማፍላት ወይም ሥራ ቦታ የተዘጋጀውን በመጠቀም ወጪን መቆጠብና ለዕዳ ክፍያ መጠቀም
  • የተለያዩ ሱሶችን በመተው በቀን ውስጥ የምናተርፈው ገንዘብ ዕዳችንን እንዲከፍል ማድረግ
  • ብዙውን ጊዜ ትንሽ የሚመስለንን የገንዘብ መጠን ነገር ግን በየቀኑ ሲጠራቀም ዕዳችንን ለመክፈል ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ማመን ይኖርብናል፡፡

እንዲሁም ማንኛውም ተጨማሪ ገቢ ያገኘነውን፣

ለምሳሌ፦

  • ትርፍ ሰዓት ወይም ሁለተኛ ሥራ ሠርተን የምናገኘው ገንዘብ
  • ከሰዎች እና ከሥራ የተሰጠን የገንዘብ ሥጦታ ወይም ቲፕ
  • በቅናሽ ከገዛነው ዕቃ ላይ ያተረፍነው ገንዘብ ተጨማሪ ገቢ እንደመሆኑ መጠን ዕዳችንን ለመክፈል ትልቅ እገዛ ያደርግልናል፡

6. ያልጠበቁትና ያላሰቡትን ገንዘብ ድንገት የሚገኝበትን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም
ስድስተኛው ያልጠበቁት ገንዘብ ድንገት ቢያጋጥምዎ፤ የደመወዝ ጭማሪ ቢያገኙ ፤ አንዴ ወጪ ሆኗል ብለው የወሰኑት ገንዘብ ቢመለስልዎ፤ ከፍ ያለ ግብር ተመላሽ (TAX RETURN) ቢሆንልዎ እነዚህንና የመሳሰሉ አጋጣሚዎችን በወቅቱ ቅድሚያ ለማይሰጣቸው ጉዳዮች ከማዋል ይልቅ ዕዳዎን መቀነስ ወይም መዝጋት የሚችሉበት ዘዴዎች ናቸው።

7. የወለድ ቅናሽ እንዲደረግልዎ በመጠየቅ
ዕዳዎን አፋጥኖ ለመጨረስ ሰባተኛው ዘዴ፤ አበዳሪዎን የወለድ ቅናሽ እንዲያደርግልዎ መጠየቅ ነው። ይህን ማድረግ እንደሚቻል ብዙዎች አያውቁም። በተለይ ደምበኛነትዎ ከአንድ ዓመት በላይ ከሆነና ፣ ክፍያዎን  በሰዓቱ ሳያቋርጡ ከከፈሉ በቀላሉ አበዳሪዎን  የወለድ ቅናሽ እንዲያደርግልዎ መጠየቅ መብትዎ ነው።  አበዳሪውም መልካም አስተያየት አድርጎ ሊተባበርዎት ይችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ዝቅተኛ ወለድ ሊሰጥዎ የሚችል ተወዳዳሪ ኩባንያ እንዳለና ቀሪ ሂሳቡዎን ወደነሱ  ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ፤ ነገር ግን ያነሰ ወይም ተመጣጣኝ ወለድ የሚሰጥዎት ከሆነ ምርጫዎ ባሉበት ኩባንያ መቆየት እንደሆነ ገልጸው ለዝቅተኛ ወለድ መደራደር ይችላሉ። ባጠቃላይ ክፍያዎን በሰዓቱና  ባለማቋረጥ እስከከፈሉ ድረስ፤ ዝቅ ያለ ወለድ ሊሰጥዎ የሚችሉ ኩባንያዎችን አወዳድረው ቀሪውን ሂሳብዎን የማዘዋወር እድል ይኖርዎታል።